Isaiah 2

የእግዚአብሔር ተራራ

1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፤

2በዘመኑም ፍጻሜ፣

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ
ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤
ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤
ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።
3ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤

“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤
እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤
በጐዳናውም እንሄዳለን።”
ሕግ ከጽዮን፣
የእግዚአብሔር ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
4እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል።
እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ፣
ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤
ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።

5እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ ኑ፤
በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ።

የእግዚአብሔር ቀን

6የያዕቆብ ቤት የሆነውን
ሕዝብህን ትተሃል፤
እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤
እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤
ከባዕዳን ጋር አገና ይማታሉ።
7ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤
ሀብታቸውም ልክ የለውም።
ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤
የሠረገሎቻቸውም ብዛት ልክ የለውም።
8ምድራቸው በጣዖታት ተሞልታለች፤
ጣቶቻቸው ላበጇቸው፣
ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ።
9ሰው ዝቅ ብሏል፤
የሰው ልጅም ተዋርዷል፤
ስለዚህ በደላቸውን ይቅር አትበል
ወይም፣ ከፍ አታድርጋቸው ማለት ነው።


10 ከእግዚአብሔር አስፈሪነትና ከግርማው ሽሽ፤
ወደ ዐለቶች ሂድ፤
በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።
11የእብሪተኛ ሰው ዐይን ይሰበራል፤
የሰዎችም ትዕቢት ይዋረዳል፤
በዚያን ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።

12የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፣
የተኵራራውን በሙሉ
የሚያዋርድበት ቀን አለው።
13ረዥምና ከፍ ከፍ ያሉትን የሊባኖስ ዝግባዎች ሁሉ፣
የባሳንን የወርካ ዛፎች ሁሉ፣
14ታላላቁን ተራራ ሁሉ፣
ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉ፣
15ረዣዥሙን ግንብ ሁሉ፣
የተመሸገውን ቅጥር ሁሉ፣
16የተርሴስን መርከቦች
ወይም የንግድ መርከቦች ማለት ነው።
ሁሉ፣
የክብር ጀልባዎችን ሁሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው።
17የሰው እብሪት ይዋረዳል፤
የሰውም ኵራት ይወድቃል፤
በዚያን ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል፤
18ጣዖቶች ሁሉ ፈጽሞ ይወድማሉ።

19 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣
ሰዎች ከአስፈሪነቱ
ከግርማውም የተነሣ፣
ወደ ዐለት ዋሻ፣
ወደ መሬትም ጕድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ።
20በዚያን ቀን ሰዎች
ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፣
የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን
ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ።
21 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣
ሰዎች ከአስፈሪነቱ
እንዲሁም ከግርማው የተነሣ፣
ወደ ድንጋይ ዋሻ፣
ወደ ዐለት ስንጣቂ ሮጠው ይገባሉ።
22እስትንፋስ አፍንጫው ላይ ባለች
በሰው አትታመኑ፤
ከቶ ምን የሚበጅ ነገር አለው!
Copyright information for AmhNASV